አማርኛ (Amharisch)

ልጄ ታሟል – እርዳታ ማግኘት የምችለው የት ነው?

ሰላም! ይህ መልዕክት በ Basel-Stadt እና Baselland ለታመሙ ህጻናት የተለያዩ የግንኙነት ቦታዎችን የተመለከተ ነው። ህጻኑ የት ትክክለኛ እርዳታ ሊያገኝ እንደሚችል ለማሳየት 4 ጥያቄዎችን እጠቀማለሁ።

ልጅዎ ታሟል እናም ልጅዎ ወደ ዶክተር መሄድ ያለበት ስለመሆን አለመሆኑ እርግጠኛ አይደሉም?

ወደ መድሃኒት መደብር ይሂዱ። ሠራተኛው የሚወሰዱ መድሃኒቶችን በተመለከተ በሚኖሩዎት የጤና ስጋቶች ወይም ጥያቄዎች ላይ ሊያማክርዎት ይችላል። ለዚህ ቀጠሮ ማስያዝ አያስፈልግዎትም። በመድሃኒት መደብሮቹ ውስጥ የተለያዩ ቋንቋዎች ይነገራሉ።
በተጨማሪም ለወላጅ የምክር አግልግሎት መስመር መደወል ይችላሉ። አማካሪዎቹ በህክምና ላይ የሰለጠኑ ሲሆን የተለያዩ ቋንቋዎችን መናገር የሚችሉ ናቸው። ልጅዎ እንዴት የላቀ ድጋፍ ማግኘት እንደሚችል ከእርሰዎ ጋር ይወያያሉ። ስለ እድገት እና ትምህርት በሚነሱ ጥያቄዎች ላይም ድጋፍ ያደርጋሉ። የወላጅ የምክር አገልግሎቶችን ስልክ ቁጥሮች እና አድራሻዎች ከ www.meinkindistkrank.ch ላይ ማግኘት ይቻላል።

ልጅዎን ወደ ዶክተር መውሰድ ይፈልጋሉ?

ከሆነ በህጻናት ሀኪምዎ ቢሮ ቀጠሮ ይያዙ። ቀጠሮውን በስልክ ማስያዝ ይችላሉ። በተጨማሪም ልጅዎ ወደ ዶክተሩ ቢሮ መሄድ ያለበት ስለመሆን አለመሆኑ በስልክ መጠየቅ ይችላሉ። እስካሁን የህጻናት ሀኪም ከሌለዎት፣ የወላጅ የምክር አገልግሎት አንድ የህጻናት ሀኪም እንዲያገኙ ሊረዳዎት ይችላል።

ልጅዎ ወደ ድንገተኛ ህክምና ክፍል መሄድ ያለበት ስለመሆን አለመሆኑና የህጻናት ሀኪምዎ ስለመኖር አለመኖሩ እርግጠኛ አይደሉም?

ከሆነ ወደ ህክምና የድንገተኛ ህመም የጥሪ ማዕከል መደወል ይችላሉ። ማእከሉ በስልክ ነጻ የምክር አገልግሎት የሚሰጥዎ ሲሆን ምሽትና የእረፍት ቀናትን ጨምሮ በቀን ለ24 ሰዓት ይሰራል። የማዕከሉ ስልክ ቁጥር 061 261 15 15 ነው።

ልጅዎ ጊዜ የማይሰጥ የህክምና እክል አጋጥሞታል?

ከሆነ ወደ የዩኒቨርሲቲው የህጻናት ሆስፒታል (UKBB) የድንገተኛ ህክምና ክፍል ይሂዱ። ችግሩ ከባድ ካልሆነ ወደ ህጻናት ህክምና ቢሮው ይደውሉ።

ልጅዎ ለህይወት አስጊ ሁኔታ ላይ ነው?

ከሆነ በቀጥታ ለአምቡላንስ አገልግሎት በስልክ ቁጥር 144 ይደውሉ።

 

ሁሉንም አድራሻዎች እና መረጃዎች ከ www.meinkindistkrank.ch ላይ በ16 ቋንቋዎች ማግኘት ይቻላል

ለእርስዎና ለልጅዎ መልካሙን ሁሉ እመኝላችኋለሁ።

ልጄ ትኩሳት ይዞታል

ምን ላደርግ እችላለሁ? ወደ ዶክተር መሄድ ያለብኝ ነው?

ሰላም! ይህ መልእክት ህጻናት ላይ የሚከሰት ትኩሳት ርዕሰ ጉዳይን የተመለከተ ነው። ትኩሳት ካጋጠመዎት እና ልጅዎ ወደ ዶክተር መሄድ ካስፈለገው ምን ማድረግ እንደሚችሉ በተመለከተ ፍንጮች እሰጥዎታለሁ።

አንድ ህጻን ልጅ በትኩሳት የሚያዘው የሰውነቱ ሙቀት መጠን 38.5 ዲግሪ ሴልሺየስ ወይም ከዚያ በላይ ሲሆን ነው። እድሜያቸው ከ3 ወራት በታች ለሆኑ ህጻናት የትኩሳት መነሻ የሰውነት ሙቀት መጠን 38 ዲግሪ ሴልሺየስ ነው። ህጻኑ ትኩሳት ሲይዘው ጉንጮቹ ይቀላሉ እንዲሁም ግንባሩ ያተኩሳል። በተጨማሪም በአዘብዛኛው የአፍንጫ ፈሳሹ ይበዛል ወይም ሌሎች ምልክቶችን ያሳያል። ሆኖም ትኩሳት አብዛኛውን ጊዜ አደገኛ አይደለም። ትኩሳት ሰውነታችንን ጤናማ እንዲሆን ይረዳዋል።

ልጅዎን በትኩሳት ሲያዝ የሚከተሉትን 5 ፍንጮች በማድረግ ሊረዱት ይችላሉ፡

  1. ለልጅዎ የሚጠጣው በቂ ውሀ እና ሻይ ይስጡት። አዲስ ለተወለዱ ህጻናት ከሆነ የጡት ወተት ወይም ፎርሙላ ወተት ይስጧቸው።
  2. ልጅዎን በቂ እንቅልፍ እንዲተኛ ያድርጉት።
  3. ልጅዎን ስስ ልብስ ብቻ ያልብሱት። ሰውነቱን በወፍራም ልብስ አይሸፍኑት።
  4. ለትኩሳት ለህጻናት የሚሰጡ ልዩ መድሀኒቶች አሉ። ለልጅዎ የትኞቹ መድሀኒቶች ጥሩ እንደሆኑ ፋርማሲ ይጠይቁ።
  5. ለልጅዎ ከፍተኛ ትኩረት ይስጡት። ለምሳሌ፡ ለልጅዎ የሆነ ጽሁፍ ሊያነቡለት ይችላሉ።

ልጅዎን ወደ ዶክተር መውሰድ ያለብዎ ስለመሆን አለመሆኑ እርግጠኛ አይደሉም? አንድ ህጻን ልጅ በሚከተሉት 8 ሁኔታዎች ወቅት ወደ ዶክተር መሄድ ያስፈልገዋል፡

  1. ህጻኑን ትኩሳት ከያዘው እና ዕድሜው ከ3 ወራት በታች ከሆነ።
  2. ትኩሳቱ ከ4 ቀናት በኋላም ካልተሻለው።
  3. ትኩሳቱ በመድሀኒት ሊቀንስለት ካልቻለ።
  4. ህጻኑ በጣም የሚዳከም ከሆነ። ህጻኑ እራሱን ከሳተ እና ህጻኑን ማንቃት ከባድ ከሆነ።
  5. ህጻኑ ፈሳሽ የማይጠጣና ዳይፐሩ ላይ የሽንት ምልክት የማያሳይ ከሆነ።
  6. ህጻኑ በጭንቅላቱ ወደፊት ማጎንበስ የማይችል ከሆነ ወይም ጭንቅላቱን ሲነካ የሚያመው ከሆነ።
  7. ህጻኑ ሰውነቱ ላይ ቀያይ ነጠብጣቦች ያሉት ሽፍታ የሚወጣበት ከሆነ። እነዚህን ሁኔታዎች መፍታት ካልተቻለ እና መፈታት የሚያስፈልጋቸው ከሆነ።
  8. ህጻኑ በትኩሳት ምክንያት ሰውነቱን ማዘዝ የሚያቅተው ከሆነ። ጡንቻዎቹ ከተንቀጠቀቀጡ፣ እራሱን የሚስት ወይም አይኖቹ የሚንቀዋለሉ ከሆነ።

 

ምን ማድረግ እንዳለብዎ አያውቁም? የወላጅ ምክር ማዕከል ወይም የህጻናት ህክምና ቢሮ ተገኝተው ይጠይቁ። ሁሉንም አድራሻዎች እና የስልክ ቁጥሮች ከ www.meinkindistkrank.ch ላይ ማግኘት ይችላሉ

ለእርስዎና ለልጅዎ መልካሙን ሁሉ እመኝላችኋለሁ!

ልጄን እያሳለው ነው

ምን ማድረግ እችላለሁ? ወደ ዶክተር መሄድ ያለብኝ ነው?

ሰላም! ይህ መልእክት በህጻናት ላይ ስለሚከሰት ሳል ርዕሰ ጉዳይ የተመለከተ ነው። ሳል ካጋጠምዎት እና ልጅዎ ወደ ዶክተር መሄድ የሚያስፈልገው ከሆነ ምን ማድረግ እንደሚችሉ በተመለከተ ፍንጮች እሰጥዎታለሁ።

ሳል የአየር ቧንቧዎችን ማጥሪያ የመከላከያ እርምጃ ነው። ጉሮሮ ይቆጣ እና አፍንጫ ንፍጥ ያመርታል። ህጻኑ አብዛኛውን ጊዜ በጉንፋን ወይም ኢንፍሉዌንዛ ስለሚያዝ ያስላል።

እነዚህ 4 ፍንጮች ልጅዎን ሳል ሲይዘው ሊረዱት ይችላሉ፡

  1. ለልጅዎ የሚጠጣው በቂ ውሀ እና ሻይ ይስጡት። የሚጠጣ ነገር ጉሮሮን ሊያረጋጋ፣ ንፍጥን ሊያላላ እና ሳልን ሊያቀል ይችላል።
  2. ሁልጊዜም ንፁህ አየር እንዲገባ መስኮት ይክፈቱ። እርጥብ አየርም ሊረዳ ይችላል። ለምሳሌ፡ ፎጣዎችን አርጥበው ማሞቂያ ላይ ሊሰቅሉ ይችላሉ።
  3. ልጅዎን በቂ እንቅልፍ እንዲተኛ ያድርጉት። የልጅዎን ከወገብ በላይ አካል ወደ ላይ ቀጥ ያድርጉ፤ ለምሳሌ፡ ጀርባውን ትራስ ላይ ሊያስደግፉት ይችላሉ። ይህ አተነፋፈስና መተኛትን ቀላል ያደርጋል።
  4. ለልጅዎ ከፍተኛ ትኩረት ይስጡት። ለምሳሌ፡ ለልጅዎ የሆነ ጽሁፍ ሊያነቡለት ይችላሉ።

ልጅዎን ወደ ዶክተር መውሰድ ያለብዎ ስለመሆን አለመሆኑ እርግጠኛ አይደሉም? ልጅዎ በሚከተሉት 5 ሁኔታዎች ወቅት ወደ ዶክተር መሄድ ያስፈልገዋል፡

  1. ህጻኑ ለመተንፈስ ሲቸገር፣ ትንፋሹ ሲቆራረጥ ወይም „ሲል የሚል ድምጽ“ ያለው አተነፋፈስ ሲተነፍስ።
  2. ህጻኑ ለ4 ቀናት ሳልና ትኩሳት ሲቆዩበት።
  3. ህጻኑ በሚተነፍስበት ወቅት ህመም ሲሰማው።
  4. ሳሉ ከ14 ቀናት በላይ ሲቆይበት።
  5. ህጻኑ ሲዳከም እና የመጫወት ፍላጎት ሲያጣ።

 

ምን ማድረግ እንዳለብዎ አያውቁም? የወላጅ ምክር ማዕከል ወይም የህጻናት ህክምና ቢሮ ተገኝተው ይጠይቁ። ሁሉንም አድራሻዎች እና የስልክ ቁጥሮች ከ www.meinkindistkrank.ch ላይ ማግኘት ይችላሉ

ለእርስዎና ለልጅዎ መልካሙን ሁሉ እመኝላችኋለሁ!

ልጄ ታሟል እና እኔ ደግሞ መስራት አለብኝ - ማድረግ ያለብኝ ምንድን ነው?

ሰላም! ይህ መልእክት ለታመሙ ልጆች በሚደረግ ክብካቤ ዙርያ የሚነሱ ጥያቄዎችን ይመለከታል። የታመመ ልጅ ለእርስዎ እንደ ወላጅ በጣም አስጨናቂ ሊሆንብዎት የሚችል ሲሆን ብዙ ነገሮችን ማመቻቸት እና ማሰብ ይፈልጋል። እዚህ ሰነድ ውስጥ በሶስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መረጃ ያገኛሉ።

  1. በህጻናት ማቆያ ማዕከላት እና ትምህርት ቤቶች ውስጥ ህመምን መቆጣጠር
  2. በስራ ቦታ እና
  3. በክብካቤ የድጋፍ አገልግሎቶች ላይ ያሉዎት መብቶች

ልጄ ታሟል። አሁንም ወደ ህጻናት ማቆያ ወይም ትምህርት ቤት መሄድ ይችላል ወይም ትችላለች?

ልጅዎ ለ24 ሰዓት ከትኩሳት ነጻ እስከሚሆን/ምትሆን ድረስ ልጅዎ ወደ ህጻናት ማቆያ ወይም ትምህርት ቤት መመለስ ላይችል/ላትችል ይችላል/ትችላለች። ይሁን እንጂ ለአንዳንድ ህመሞች ልዩ ደንቦች ተፈጻሚ ይሆናሉ። ዝርዝር የመፍትሄ ሃሳቦችን የያዘ በራሪ ወረቀት ከሚከተለው አድራሻ ሊገኝ ይችላል www.meinkindistkrank.ch

ለ Basel-Stadt: richtlinie-infekt-krankheiten-2024.pdf (bs.ch)

ለ Baselland: መመርያዎች (webcloud7.ch)

ልጄ ታሟል እና እኔ ደግሞ መስራት አለብኝ። ማወቅ ያለብኝ ምንድን ነው?

እርስዎ እንደ አባት ወይም እናት ልጅዎን ለመንከባከብ ህመም በተከሰተ ጊዜ ቢበዛ ለሶስት ቀናት ቤት መቆየት እንደሚችሉ ህጉ ይደነግጋል። በነዚህ ሶስት ቀናት ውስጥ ተገቢውን ክብካቤ ለማመቻቸት መሞከር አለብዎት። ልጁ ዘለግ ላለ ጊዜ ከታመመ እና ሊገኝ የሚችል ሌላ ክብካቤ ከሌለ፣ አሰሪዎን ማናገር የሚያስፈልግዎ ሲሆን የእረፍት ፈቃድ ቀናትን ወይም ትርፍ ሰዓት ሊጠቀሙ የሚችሉበት እድል ይኖራል።

በሀኪም የተሰጠ ማስረጃ ሊያስፈልግዎ ይችላል። በናንተ ኩባንያ ውስጥ ተፈጻሚ የሆኑት የትኞቹ ደንቦች እንደሆኑ አሰሪዎን ይጠይቁ።

እኔ መስራት ያለብኝ ሲሆን ልጄን ሊንከባከብ የሚችል ሌላ ሰው የለም። ምን ምን አማራጮች አሉኝ?

የስዊዘርላንድ ቀይ መስቀል ቤትዎ የሚመጡ የሰለጠኑ እና ልምድ ያላቸውን ሰራተኞች ይመድባል። ለልጅዎ ክብካቤ እና ክትትል ይደረግለታል። ሠራተኛው ምግቦችን ያዘጋጃል፣ ከልጅዎ ጋር ይጫወታል እንዲሁም ከርስዎ ጋር በመመካከር መድሃኒት ይሰጠዋል። ይህ አገልግሎት እድሜያቸው እስከ 12 ዓመት ለሆናቸው ልጆች የሚፈጸም ሲሆን ክፍያ ይከፈልበታል። አንዳንድ የጤና መድን ዋስትና ኩባንያዎች ለነዚህ ወጪዎች ሽፋን ይሰጣሉ። የጤና መድን ዋስትና አቅራቢዎን ይጠይቁ። የስዊዘርላንድ ቀይ መስቀልን ዝርዝር የመገናኛ አድራሻ ከሚከተለው አድራሻ ማግኘት ይችላሉ www.meinkindistkrank.ch.

Rotes Kreuz Basel-Stadt: 061 319 56 51, https://www.srk-basel.ch/entlastung-1/familienentlastung

Rotes Kreuz Baselland: 061 905 82 19, https://www.srk-baselland.ch/fuer-sie-da/entlastung/familienentlastung

ለእርስዎና ለልጅዎ መልካሙን ሁሉ እመኝላችኋለሁ!